የኮንስትራክሽን ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋሙ አመራርና ሰራተኞች

የኮንስትራክሽን ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋሙ አመራርና ሰራተኞች

የፐብሊክ ሰርቪስና የሲቪል ሰርቪስ ቀንን በጋራ አከበሩ

የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ዋናው መ/ቤትና ለእሱ ተጠሪ የሆነው የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አመራርና ሰራተኞች 10ኛውን የፐብሊክ ሰርቪስና የሲቪል ሰርቪስ ቀን ሐምሌ 19 ቀን 2008 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል በታላቅ ድምቀት አከበሩ፡፡

የበዓሉ አከባበር ከፊል ገጽታ

በዓሉ በኮንስትራክሸን ሚኒስቴር ሚኒስትሩ በክቡር ዶ/ር አምባቸው መኮንን የእንኳን ደህና መጣችሁ የመክፈቻ ንግግር የተከፈተ ሲሆን የኢትዮጵያን ህዝብ መዝሙር በጋራ በመዘመርና የዳቦ ቆረሳና የሻማ ማብራት ሥነ-ስርዓት ከተካሄደ በኋላ ለፓናል ውይይት የሚረዳ እለቱን የሚዘክር የመነሻ ጽሁፍ በኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የለውጥ ሥራ አመራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በአቶ መላክ አለሙ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ከየት ወደ የት በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ለቀደሙት ዘመናት ካረጀው ስርዓት ጀምሮ አሁን እስካለንበት ደረጃ ድረስ ያለውን ሁኔታ በሚያሳይ መልኩ እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡

በመቀጠልም በኤችኤቪ/ኤዲስ ወላጆቻቸውን ያጡና አሳዳጊ የሌላቸውን ህጻናት ለመደገፍ የሚያስችል መነሻ ጽሁፍ በስርዓተ ጾታ ሜኒስትሪሚንግ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ በአቶ ከተማ ሚዲቅሳ አማካኝነት ቀርቧል፡፡

የቀረበውን መነሻ ጽሁፍ ተከትሎ ክቡር ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ዛሬ የምንሰራቸው ሥራዎች የወደፊት የእርካታችን ምንጭ ስለሆኑ አኩሪ ታሪክ ለመስራት ዕድሉ በእጃችን ነው፡፡ ይህን ስናደርግ ስር የሰደደውን ድህነት ከስሩ ለመንቀልና ከተገኘው ውጤት ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበትንና ጎዳና ላይ የተበተኑ ህጻናት ከአስከፊው ህይወታቸው ተላቀው የተሻለ ህይወት እንዲመሩ ማድረግ ያለብን መሆኑን በመግለጽ ይህንን በዓል ስንዘክር መላ ትኩረታችን ማህበራዊ ቀውስን መመከትና ልማትን ማፋጠን ስለሆነ በዚህ አግባብ እንወያይ የሚለው የክቡር ሚንስትሩ የውይይት አቅጣጫ ሆኖ በዚሁ አግባብ ውይይት ተደረጎ  በቀረቡት የመነሻ ጽሁፎች ዙሪያ ጥያቄና አስተያየቶች ቀርበው የጋራ መረዳት ላይ ከተደረሰ በኋላ ለተጠየቀው ድጋፍ ሁሉም ሠራተኛ ከወር ደመወዙ በቋሚነት ከ0.5 በመቶ ጀምሮ በፍላጎት ላይ የተመሠረተ ደጋፍ ለማድረግ መግባባት ላይ ተደርሶ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡