የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አመራርና ሠራተኞች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሄዱ

የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አመራርና ሠራተኞች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሄዱ

የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አመራርና ሠራተኞች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይና የኮንስትራክሽን  ፖሊሲን ለማስፈጸም በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያ የጋራ ግንዛቤን በመያዝ ወደስራ ለመግባት በሚያስችላቸው ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት ጥቅምት 3 ቀን 2009 ዓ.ም በሚኒስቴር መ/ቤቱ 8ኛ ፎቅ አዳራሽ አካሄዱ፡፡

ፕሮግራሙ በሬቻ በዓልና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት ህይወታቸውን ላጡ ዜጎቻችን የህሊና ጸሎት በማድረግ የተጀመረ ሲሆን መድረኩን በንግግር የከፈቱት ደግሞ ክቡር ዶ/ር አምባቸው መኮንን የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር ናቸው፡፡

ክቡር ሚኒስትሩ በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ እንደተናገሩት የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱ የጋራ ግንዛቤን በመያዝ ሚኒስቴር መ/ቤቱ የተጣለበትን ተግባርና ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት የሚያስችለውን ተግባር ለማከናወን የሚረዳው መሆኑን ገልጸው ውይይቱ የታለመለትን ዓላማ ሊያሳካ በሚችልበት ሁኔታ ላይ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚስፈልግ ገልጸዋል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዙሪያ የተዘጋጀውን መነሻ የውይይት ሠነድ ያቀረቡት የሚኒስቴር መ/ቤቱ የህግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አበረ አስፋው ሲሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከህግ አኳያ ያለውን ተገቢነት በተመለከተ መንግስት የሰጠው መግለጫ ተገቢና ከህግ አኳያም ተቀባይነት ያለው መሆኑን በገለጻቸው አስታውሰው ልማታችንን ለማስቀጠልና የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መውጣቱ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

       የመድረኩ ተሣታፊዎችም ከቀረበው ገለጻ በመነሳት የተለያዩ ሀሳብ፣ አስተያየቶችና ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን ከቀረቡት አስተያየቶች መካከልም  በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ሁከትና ግጭቶችን ወደነበሩበት መመለስ ቢቻልም የዲሞክራሲ ግንዛቤው በሀገራችን እምብዛም ያልዳበረ በመሆኑ ከውጭ ተስበው የመጡ ኢንቨስትመንቶች ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመከላከልና የህዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ ጉዳዩ በጥበብም መመራት ስላለበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊወጣ ችሏል፡፡ በዚህም ሀገራችን ወደነበረችበት የልማት፣ የሰላምና የዲሞክራሲ መደበኛ ሁኔታ እንድትመለስ ለማድረግ ታስቦ ነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የወጣው የሚለው ሀሳብ ሁሉንም ያግባባ ነበር፡፡

      ከቀረቡት ጥያቄና አስተያየቶች መካከል፡-

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፓርላማ ሳይጸድቅ ተፈጻሚ ሊሆን ይችላል ወይ? የሚል ጥያቄ ተነስቶ ፓርላማው በስራ ላይ ካለ በ24 ሰአት ውስጥ፤ ፓርላማው ዕረፍት ላይ ከሆነ ደግሞ በ15 ቀን ጊዜ ውስጥ ይጸድቃል፡፡ ከአስቸኳይነት አንጻር ግን ሚኒስትሮች ምክር ቤት በተሰጠው ስልጣን መሠረት ውሳኔው ተፈጻሚ እንዲሆን ማድረግ ይችላል የሚል ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

ዕድገት ሲኖር የተቃውሞ ቀውስ እንደሚኖር ይጠበቃል ያሉት አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የወጣው ባላወቅነው ሁኔታ መናጆ እንዳንሆን፣ መረጃ እንድንመርጥና ለሌሎችም ማሳወቅ እንድንችል ነው፤ ትርምስን በመፍጠር ፍላጎትን ማሳካት እንደማይቻል ቢታወቅም ሁከትና ብጥብጥ መፍጠር ልማትን ከማደናቀፍ ባለፈ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም፤ ስለሆነም ይሄን የመመከት ተልዕኮ ለአንድ አካል የምንሰጠው ተግባር ሳይሆን የሁላችንንም ርብርብ የሚጠይቅ ስለሆነ እያንዳንዳችን ወቅታዊ ሁኔታዎችን ለማገናዘብ ከራሳችን ጋር መምከር አለብን ብለዋል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በህዝብ ዘንድ እንዲሰርጽ ለማድረግ እስከ ቀጠናና ወረዳ ድረስ ቢሰራ፣ ኮማንድ ፖስቱን መስለው ህዝብን እንዳያጠቁ በህብረተሰቡ ውስጥ ስጋት አለና በየአካባቢው ያለው የአዝማሚያ ቅኝት ቢጠና የሚል አስተያየትና ኮማንድፖስቱ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ተደራሽ መሆን ይችላል ወይ የሚለውን ጥያቄ አንስተዋል፡፡

እነዚህና መሰል ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከተሰጡ በኋላ በክቡራን ሚኒስትሮች ምላሽና የማጠቃለያ አስተያየት ተሰጥቶበት ፕሮጋራሙ ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡