በግንባታ አካላትና በተገጣጣሚ ህንፃ አካላት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ

በግንባታ አካላት ማምረቻ፤ እንዲሁም በተገጣጣሚ ህንፃ አካላት ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገ የአንድ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ የካቲት 16 ቀን 2009 ዓ.ም በፍሬንድሺፕ ኢንተርናሽናል ሆቴል ተካሄደ፡፡ 

በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ ከፌዴራልና ከክልል የተውጣጡ የአስፈጻሚ አካላት ተወካዮችና በዘርፉ ከተሰማሩ ኩባንያዎች የተወከሉ ተሣታፊዎች የተገኙ ሲሆን መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የአቅም ግንባታና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው ክቡር አቶ ገ/መስቀል ጫላ ናቸው፡፡

ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በመክፈቻ ንግግራቸው፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገሮች ግንባር ቀደም ከሆኑት ዘርፎች ማለትም ከግብርና፤ ከትምህርት፤ ከጤናና ከመሰረተ ልማት ተርታ የሚመደብ እንደሆነና በተለያዩ ዘርፎች መጠነ-ሠፊ የሆነ ሀብትን የሚያበዛ፤ ከዚህም ዜጎችን ተቋዳሽ የሚያደርግ፤ በአጠቃላይም ለምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት የላቀ ሚና የሚጫወት ግዙፍ ዘርፍ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በማያያዝ ከ1994 ዓ.ም ወዲህ በመኖሪያ ቤቶች፤ በመንገድ፤ በኃይል እና በባቡር ልማት ፕሮግራሞች፤ እንዲሁም በሌሎች ግዙፍ ኢኮኖሚያዊ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚነትን ያሳደጉ ተጨባጭ የሆኑ ውጤቶች መመዝገባቸውንና ኢንዱስትሪው ካስመዘገባቸው የልማት ውጤቶች ጎን ለጎን በመንግስት እና በግሉ ዘርፍ በሚከናወኑ ሰፋፊ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች አማካኝነት ለዜጎች የተፈጠረው የሥራ ዕድል ወደ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ማደጉ ኢንዱስትሪው በቀጣይ የዜጎች የኑሮ መሠረት መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

በተነጻጻሪ ፍሬያማ ውጤቶች የመኖራቸውን ያህል ኢንዱስትው በሚፈለገው ፍጥነት አለማደጉንም አልሸሸጉም፡፡ የክፍተቶቹ  መንስኤዎችም  የማስፈፀምና የመፈፀም አቅም ውሱንነት፤ የግብኣት አቅርቦት ክፍተት፤ የምርታማነትና የጥራት ጉድለት፤ የቴክኖሎጂ አለመስፋፋት፤ እንዲሁም ወጥነት ያላቸው የአሰራር ሥርዓቶች አለመዘርጋታቸው መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

እነዚህን ተግዳሮቶች ለማስወገድ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በአቅም ግንባታ ፕሮግራሙ በዋናነት የኢንዱስትሪውን የባለሙያዎች፤ የስራ ተቋራጮችና የአማካሪ ኩባንያዎች፤ የግንባታ ግብዓት አምራቾችና አቅራቢዎችን የመፈፀም ብቃት ለማጎልበት ከያዛቸው ዕቅዶችና ግቦች መካከል የህግ ማዕቀፎችን ከማሻሻል ጎን ለጎን የግንባታ አካላትን ለመለየት የሚረዳ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ የሚታዩ ክፍተቶችን ማጥበብ፤ የኮንስትራክሽን አካላት ማምረቻ ተቋማትን ለማደራጀት የሚስፈልጉ የአሰራር ስርዓቶችን መዘርጋት እና በግንባታ አካላት ላይ በቂ ግንዛቤን በማስጨበጥ በዚህ ዘርፍ የተሰማሩና የሚሰማሩ ባለሀብቶች የሚደገፉበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡

ተሣታፊዎችም በቀረቡት ሦስት ሰነዶች ላይ በመመስረት የየበኩላቸውን አስተያየት ያቀረቡ ሲሆን ከቀረቡት  ሀሳብና አስተያየቶች ዋና ዋናዎቹ፡- ቴክኖሎጂን የማላመድ ችግር፣ ገበያውና አምራቾች የሚገናኙባቸው የቴክኖሎጂ መንደሮች አለመኖር፣ በመስኩ የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግር፣ የግንባታ ሥራውን ከባህላዊ አሠራር ወደዘመናዊ ለመቀየር አለመቻል፣ ከሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችን ለማምጣት ተቀናጅቶ ያለመስራት ችግር እንደሚታይ ገልጸው በመፍትሄነት ደግሞ የተገጣጣሚ ህንጻ አካላትን ግንዛቤ ማሳደግ፣ ከሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችን ማበራከት፣ የትብብር መድረኮችን ማሳደግ፣ መንግስት የመሪነት ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ ማድረግ፣ ፈጠራን በማበረታታት የፈጠራ ባለቤትነት ስርቆትን ማስወገድ፣ ከሰርክል ውጪ በማሰብ ውስብስብ ዲዛይኖችን ማስወገድ፣ የጎረቤት አገር ገበያን አስከመጠቀም ማሰብ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወደአገር ውስጥ በማስገባት የማላመድ ሥራን መስራት፣ ባህላዊውን የአሠራር ባህል መስበርና አዳዲስ አሠራርን ለመቀበል የሚያስችል አቅም መፍጠር፣ ጠንካራ አመራር መፍጠር፣ ከዘልመድ አሠራር የሚያወጡ አስገዳጅ ሁኔታዎችን ማስቀመጥ፣ በዘርፉ የሚታዩ ጉድለቶችን ማስተካከል፣ በተገጣጣሚ ህንጻ ቴክኖሎጂ ላይ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች በቂ የፋይናንስ ድጋፍ መስጠት የሚሉት ነጥቦች ተነስተዋል፡፡

በመንግስት በኩል በተገጣጣሚ ህንጻ ቴክኖሎጂ ላይ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች እስከ 85 በመቶ የሚደርስ የፋይናንስ ድጋፍ በልማት ባንክ በኩል የሚሰጥ ቢሆንም እስካሁን ድረስ በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎች ብዛት ከአምስት እንደማይበልጥ በገለጻው ወቅት የተነሳ ሲሆን ህብረተሰቡ በተገጣጣሚ ህንጻ አካላት የሚገነቡ ህንጻዎች ጊዜና ወጪ ቆጣቢ መሆናቸውንና  በባህላዊ መንገድ በሳይት ላይ የሚገነቡ ህንጻዎች ከ20 በመቶ በላይ ብክነት የሚያስከትሉ መሆናቸውንና ይህን  ለመከላከል የሚያስችሉ ከመሆናቸውም በላይ ከአካባቢ ብክለት የጸዳ አሠራርን ለመከተልና የጥራት መጓደልን ለማስቀረት እንዲሁም ስታንዳርድን ለማሟላት የሚያግዝ ከመሆኑ አንጻር ገበያውን ለማስፋትና በግንባታ ሂደት የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ስለተገጣጣሚ ህንጻ አካላት ግንባታ የህብረተሰቡ ግንዛቤ አድጎ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሚፈለግበትን ውጤት እንዲያሳካ ሠፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሰራት እንዳለባቸው መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡