አዲስና ነባር አመራሮች የስራ ርክክብ አደረጉ

በአዲስ መልክ የተዋቀረው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽ ሚኒስቴር አዲስ እና ነባር ከፍተኛ አመራሮች ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ.ም ትውውቅና የስራ ርክክብ አካሄደዋል፡፡
በቀድሞው የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ጽ/ ቤት በተካሄደው የትውውቅና የስራ ርክክብ ስነስርዓት ላይ ክብርት ኢንጅነር አይሻ መሐመድ ( አሁን የሀገር መከላከያ ሚኒስትር) ቀደም ሲል የሚኒስቴር መስሪያቤቱ የተጓዘባቸውን የተግባር ሂደቶች ለአዲሶቹ ከፍተኛ አመራሮች ገለፃ አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም በሀገር ደረጃ ዘርፉ መጫወት የሚገባቸውን ሚናዎች አስመልክቶ እየተከናወኑ የነበሩ፣ የተከናወኑ እና በጅምር ላይ የሚገኙ ቁልፍ ተግባራትን አብራርተዋል፡፡ በቀጣይም አዲሱ ከፍተኛ አመራር ትኩረት ቢያደርግባቸው ያሏቸውን ጉዳዮችም ክብርት ኢንጅነር አይሻ መሐመድ አስረድተዋል፡፡
በአዲስ መልክ የተዋቀረው የከተማ ልማትና የኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ ክቡር አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው አዲሱ ሚኒስቴር መስሪያቤት በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ወደተግባር መግባት የሚያስችሉ ተግባራት በፍጥነት እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ሁለቱ ሚኒስቴር መስሪያቤቶች ወደ አንድ መጡ እንጂ የፈረሰ ተቋም አለ ማለት እንዳልሆነ ሁሉም አካል ተገንዝቦ ስራዎች በተጠናከረ ሁኔታ እንዲቀጥሉ እንዲደረግም አስምረውበታል፡፡ የአዲሱ አደረጃጀት በፍጥነት መልክ እስከሚያዝ ድረስ ግን የቀድሞው ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ባለበት ጽ/ቤት ሆኖ በአዲሱ አመራር እየተመራ ዕቅዶች በውጤታማነት እንዲፈፀሙ ርብርብ እንደሚደረግም ክቡር ሚኒስትሩ አቶ ጃንጥራር አባይ አስገንዝበዋል፡፡
ክብርት ኢንጅነር አይሻ መሐመድ የቀድሞውን የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የስራ አቅጣጫዎችን የያዘ ሰነድ ከክቡር አቶ ጃንጥራር አባይ ጋር ርክክብ አድርገዋል፡፡ 
አዲስ እና ነባር ሚኒስትሮች የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች፣ ኩባንያዎችና መሳሪያዎች ምዘና እና ብቃት ማረጋገጫ ቢሮ ስር የሚገኙትን የስራ ክፍሎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡: